ጭንቀቴ መች ገባሽ
from Sost kilo Hosted by Leoul Zewelde
…ጭንቀቴ… ድር እንዳጠመደው ዝንብ ነው ። ሸረሪቷ ካሁን አሁን መጣች እያለ እንደሚሳቀቅ … ክንፉን እያማታ… የትም እንደማይፈናፈን… …ጭንቀቴ…ለወር ታህል ቋጥራ እንደሚሾትልባት ነብሰጡር ነው ። ማህፀኗ አልረጋ እንዳላት … ዘጠኝ ወር ርቆ … የምልጃዋን ማርያም … ማርያም እንደምትል … ጭንቀቴ…ከእናት አባቱ ጥል አምልጦ እንደወጣ ህፃን ነው ። … የሚሮጥ መድረሻ የሌለው… ልጋጉን እየሳበ በለንባዳ አፉ እንደሚያለቅስ … …ጭንቀቴ … ፈረሰኞች በሌት መጥተው ጎተራውን እንዳነደደቡበት መጤ ነው ። ነጋጠባ ውጣልን እንደሚባል … ከአመድ ክምር ላይ ተቀምጦ… በለበቅ መሬት እንደሚጭር … …ጭንቀቴ… ደግመው ደጋግመው እንደደፈሯት ማቲ ነው ። በወሲብ ያጋሱባትን ስታይ ወደውስጥ ያነባችው እንደሚንጣት… ሽንቷ እንደሚሞቃት … …ጭንቀቴ… የብርሃን መቅረዙን ሰም እንደሞላው ምስኪን ነው ። ከእንቅልፉ ሲነቃ አይኑ እንደተጋረደበት … ድንገት ማየት እንደተሳነው … ታውሮ ታገኘው እንደሚላተም … …ጭንቀቴ… ምላሠ ጥቁር ረግሟት የሚያረክስላት ደብተራ እንዳጣች ጋለሞት ነው ። የነካችው ሁሉ አልሰምር ብሎ … ህይወቷ ቆሌ እንዳጣባት… …ጭንቀቴ… ተፈርጆ እንደተያዘተ ግዞተኛ ነው ። ሊያርዱት አንበርክከው የኋሊት እንደጠፈሩት … ከገላው ላይ የሥለት ንኺ እንደሚጠብቅ… …ጭንቀቴ … ከጠባቂዋ ባልጋ የወር አበባዋ እንደቀረባት ልዕልት ነው ። የአባቷ ዘውድ እንዳይሰደብ መታነቂያ ቃጫ እንደምትፈትል … ነብሷን ልትሸኝ አንድ ሐሙስ እንደቀራት… …ጭንቀቴ… እንደወደቀ የክፍል ተማሪ ነው ። ተከልሶ ከጓደኞቹ ኋላ እንደቀረ … እንደፈራ መስከረም እንደደረሰበት… …ጭንቀቴ… ደመና አልፎት እንዳይሄድ እንደሚፀልይ ገበሬ ነው ። ረሀብ ሊፈጀው ጥፍሩን ስሎ እንደመጣበት … የቀበረውን ዘር ቆፍሮ ሊቅም እንደተቃጣ … …ጭንቀቴ… እርሙን እወድሻለው ብሎ …እሺ… እንደተባለ አፍቃሪ ነው ። " እሺ " ደግሞ ምንድነው እያለ እንደሚብሰለሰል … ስሜትሽን ማወቅ ሽቶ ፥ እንዳልተነገረው …የተወሰደበት …እንደማይሰጠው … መጨነቄ መች ገባሽ ።
Embed this episode
No transcript yet.